የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአረንጓዴ አሻራ “አንድ ሰው 100 ችግኝ የመትከል መርሃ ግብርን” ጀመረ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፤ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሠራተኞች በእንጦጦ የአፍሪካ የስፔስ ማዕከል ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን አከናውነዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒ ኤች ዲ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ፒ ኤች ዲ) በግለሰብ ደረጃ 100 ችግኞችን ለመትከል ያስቀመጡትን አቅጣጫ በመቀበል የአረንጓዴ አሻራችንን እናሰቀምጣለን ብለዋል።

በኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና ምርምር መስክ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን ከመትከል በዘለለ የመንከባከብና ክትትል የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይረክቴር አቶ አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ዓላማ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራምን በጋራ እውን ከማድረግ ባለፈ “እኛ እና እነሱ” የሚባለውን እሳቤ በመስበር አንድነታችን ለማጠናከር ነው ብለዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በክረምት የበጎ አድራጎት ስራ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስና ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ የማሟላት ስራ እንደሚሰራ አስታውቋል።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በቀጣይ በሌሎች ቦታዎችም ይከናወናል።ከዚህ ጎን ለጎን ለአፍሪካ የስፔስ ማዕከል ግንባታ በተረከበው 16ሺህ ካሬ መሬት ጦም እንዳያድርና ለአርሶ አደሩ አርዓያ ለመሆን 24 ኩንታል የሚደርስ ገብስ እየተዘራ ሲሆን ከዚህም 800 ኩንታል ገብስ ምርት ይጠበቃል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook