የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ቪዛ በኢትዮጵያ ዲጂታይዜሽንን ለማሳለጥ የሚረዳ ስምምነት አደረጉ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ዓለም አቀፉ የክፍያ ቴክኖሎጂ ተቋም ቪዛ ዲጂታይዜሽንን ለማስተዋወቅና ለማሳለጥ እንዲሁም የፋይናንሽያል ቴክኖሎጂ ድርጅቶችን ለመደገፍ “ቪዛ በማንኛውም ስፍራ” የተሰኘ ኢኒሽየቲቭ ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ፤ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) የኢትዮጵያ መንግስት አካታች የፋናንስ ስርዓትን ለመገንባት ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት እንደሚያምንና ይህን እውን ለማድረግም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የተሰኘ ጠንካራ ስትራቴጂ መቅረፁን ተናግረዋል፡፡

ይህ ስትራቴጂ ለህዝብ፣ ለመንግስትና ለንግዱ ማኅበረሰብ የክፍያ ስርዓቶች በስፋት ለማቅረብ የሚያስችልና ዲጂታይዜሽንን እንደ ቁልፍ እርምጃ ያስቀመጠና ግቡም አድርጎ የወሰደ ነው ብለዋል፡፡

የቪዛ ምክትል ፕሬዘዳንትና ከሰሀራ በታች ላሉ ሀገሮች የድርጅቱ ኃላፊ አይዳ ዲያራ “ይህ አጋርነት ድርጅታችን ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ያለውን ቁርጠኝነት በጉልህ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋማት አስቻይ ስርአትን ለመገንባት በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘች ነው ያሉት ኋላፊዋ በተቋማችን ቪዛ በሁሉም ስፍራ እንከን የለሽ በሆነ መንገድ ገንዘብ ማስተላለፍ እንዲኖር መፍትሔ ለሚያበጁ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ መስጠት ዋነኛ ግባችን ነው ብለዋል፡፡

ቪዛ በተናጠል በአዲስ አበባ የሚገኝ የዲጂታል ሚዲያና ዳታ፣ በኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ዙርያ በትኩረት የሚሰራ ሸጋ ሚዲያና ቴክኖሎጂ ኃ/የተ/የግል ማኅበር በጋራ በመሆን “ቪዛ በማንኛውም ስፍራ 2021” የተሰኘውን ፕሮግራም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በዚህ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ቪዛ ስልጠና እና የአቅም ግንባታ ስራዎች እንዲሁም በሀገሪቱ ያሉ የዲጂታይዜሽን እድሎችን የመለየትና የመፈተሸ ስራም በጋራ ሲሰሩ፤ ሸጋ “ቪዛ በማንኛውም ስፍራ 2021” የተሰኘውን ፕሮግራም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook