የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሃመድ (ፒ ኤች ዲ)፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሚ እና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህወይት ወልደሃና (ፒ ኤች ዲ) የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
ድርጅቱ ከቡና አተላና ገለባ፣ ከጫት ገረባ፣ ሳጋቱራና ከመሳሰሉት የቆሻሻ ውጋጆች ሃይል መስራት የሚያስችል እና ይህንን የሚጠቀም ስቶቭ እያመረተ ይገኛል።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ማብሰያዎች ከአካባቢ ጋር የሚስማሙና ፍጆታን የሚቀንሱ ናቸው።
ከቆሻሻ ውጋጅ የሚገኘውን ሃይል እና ማብሰያውን የሚያመርተው ድርጅቱ በቀን እስከ 200 የሚደርስ “ቋይቶን” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ስቶቭ የማምረት አቅም ላይ ደርሻለሁ ብሏል።

የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ፀጋየ ነጋ የቋያቶንን ንድፍ (design)፣ እቃውን መፈብረክና ለቋይቶን የሚሆን ተቀጣጣይ በአንድ ላይ በማምረት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ውስጥ ብቸኛ ነን ብለዋል።
ተቀጣጣዩ ለማብሰያነት ካገለገለ በኋላ ወደ ከሰልነት የሚቀየር ሲሆን ድርጅቱ ይህንን ከሰል ከደንበኛው ድጋሚ በመግዛት ስራ ላይ ያውለዋል።
በብዛት ለምግብነት የሚሰራን ወጥ ምሳሌ ያደረጉት ፕሮፌሰሩ 100ሊትር ወጥን ለማብሰል 6 ሰዓት ይፈጅ የነበረውን የማብሰያ ጊዜ ወደ 1 ሰዓት የሚያወርድ ማብሰያም መስራታቸውን ጠቁመዋል።
በቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ ፓርክ እየሰራ የሚገኘው ይህ ድርጅት በፓርኩ ውስጥ የተሰጠውን የመስሪያ ቦታ ልቀቅ በመባሉ ምክንያት ስጋት እንዳደረበት ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ ተቋማቸው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን የሚያደግፍበት “የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች አዋጅ” (startup proclamation) አዘጋጅቶ መፀደቁን እየተጠባበቀ መሆኑንና ይህ አዋጅ እንዲህ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታ ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሚ በበኩላቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ድርጅቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የመስሪያ ቬድ ኪራይን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግለት ቆይቷል።
ከሰሃራ በታች 600ሚሊየን አካባቢ የስቶቭ ፍላጎት ያለ ሲሆን በዘርፉ የተሰማሩ በጣት የሚቆጠሩ ተቋማት ብቻ ናቸው።