ልዑካኑ ዓለም አቀፉን የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ለመካፈል አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን የኢትዮጵያን የተሳካ ዝግጅት አድንቀዋል።በውይይታቸው በዲጂታላይዜሽን፣ በግል ዴታ ጥበቃ እና ከበይነ-መረብ ግንኑነት ውጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማገናኘት እና በሌሎችም የትብብር ዘርፎች ላይ አተኩረው ተነጋግረዋል።
የጀርመን ልዑካን በቅርቡ ሀገራቸው ስላፀደቀችው የዲጂታል ስታራቴጂ እና የዲጂታል ክፍፍል የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ በኩልም ኢትዮጵያ አፅድቃ ወደ ስራ ባስገባችው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እና ስትራቴጂው ቅድሚያ ሰጥቶ እየተሰራባቸው ስላሉ ጉዳዮች ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በጀርመን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የመረጃ መረብ አምባሳደር ሬጊን ግሪንበርገር (ፒ ኤች ዲ) ኢትዮጵያ ሰላዘጋጀችው የግል ዴታ ጥበቃ አዋጅ እና በጦርነቱ ምክንያት ከበይነ-መረብ ግንኙነት ውጭ የሆኑ አካባቢዎችን ማገናኘት ላይ እየተሰራ ስላለው ስራ ጠይቀው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ የግል ዴታ ጥበቃ አዋጁ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ የወሰደና የዜጎችን የግል ዴታ በሚያስጠብቅ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት ምክንያት አገልግሎት በተቋረጠባቸው አካባቢዎች መልሶ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ መንግስት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች መብራት፣ ስልክና ውሀን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶች በመመለስ ረገድ እንዲሁም የመድሀኒትና የምግብ አቅርቦት ላይም ስራ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልል እንዲሁም በፀጥታ ችግር ምክንያት በይነመረብ አገልግሎትን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎት በተቋረጠባቸው በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለሰላም ቁርጠኝነትን አሳይተዋል ያሉት ሚኒስትሩ በህወሃት በኩል ለዚህ ቁርጠኝነት እውቅና በመስጠት ለፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈፃሚነት ከሀቅ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረው በህወሀት ውስጥ የሚታየውን የተደባለቀ አካሄድና ከዚህም ሲያልፍ በደጋፊወች ብሎም በግማሽ አካል አመራሮች የሚታየው የቀጠለ የጦረኛነት ፍላጎት የሠላሙን ጥረት ወደኋላ እንዳይመልሰው ስጋታቸውን በመግለጽ፣ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የጀርመን መንግስት በህወሀት በኩል ያለውን የተደባለቀ እንቅስቃሴ አቃለው እንዳያዩት አሳስበዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የአውሮፓ ህብረት እና የጀርመን መንግስት ውስብስብ የሆነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ በውል እንዲገነዘቡና ለኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ድጋፍ እንዲያሳዩ ጠይቀዋል። በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል።