የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል እውቀት ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጠየቀ።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለትምህርት ዘርፉ በሚያደረገው አስተዋጽኦ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲካሄድ የቆየውና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ተጠናቅቋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ያኒአ ሰይድመክይ (ፒ ኤች ዲ) በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ኢትዮጵያ የያዘችው እቅድ እንዲሳካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል እውቀት ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ወደ ተግባር የሚለወጠው ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የዲጂታል እውቀትና ክህሎት ላይ ሲሰሩ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የቴክኖሎጂ አፍላቂዎችን በመለየት፣ ስራዎቻቸው እንዲወጡና ወደ ማህበረሰቡ እንዲወርዱ ማድረግ ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋልም ተብሏል።

በውይይቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በትምህርት ዘርፍ፣ የዲጂታል ክህሎት ፍኖተ ካርታ አተገባበር፣ መጻኢ ቴክኖሎጂዎች በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያላቸው ፋይዳ እና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዘርፉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ፣ የኢኖቬሽን ፈንድ አዋጅ፣ የትራንዛክሽን አዋጅ፣ የዲጂታል ክፍያና የመሳሰሉትን ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook