ዲጂታል ስትራቴጂ

ዓለም ባልተጠበቀ ፍጥነት አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት እያካሄደች ትገኛለች። ማኅበረሰባችን ከዚህ ክስተት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማረጋገጥ እና ወጣቶቻችን በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ስኬታማ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ በንቃት መሥራት ይጠበቅባታል። በአሁኑ ወቅት እንደ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Arteficial Intelegence)፣ የበይነ መረብ ቁሶች (Internet of things)፣ ናኖ ቴክኖሎጂ፣ እና ውሒብ አስተኔ (Big Data) ባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚደገፉ የማምረት፣  የመገናኛእና የአኗኗር ዘዬ ሽግግርን እየተመለከትን ነው።  ታዳጊዎች አዳዲስ ክሂሎት እና ዕውቀቶችን ይፈልጋሉ ፤ የወደፊቱን ጊዜ በተሻለ ለመጠቀም እንዲችሉ የማድረግ  ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው።

ኢትዮጵያ ዲጂታል ከባቢ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጸገ ኅብረተሰብን ለመገንባት የሚያስችላትን አቅም ገና አልፈጠረችም። ዐቅምን በማጠናከር ስኬታማ ለመሆን ደግሞ ፈጣን ፣  እና ልበ-ሙሉ የተቀናጀ ርምጃ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን ። በ2011 ዓ.ም. ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ አጀንዳ እና የአሥር ዓመት ብሔራዊ የልማት ዕቅድ (2011-2021) አጽድቀናል። አዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ዕድገትን ዘላቂ ለማድረግ እና እያንዳንዱ ዜጋ ከሀገር አቀፍ ብልጽግና ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ዕድል ይሰጣሉ።

እነዚህን የዲጂታል ከባቢ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም የመንግሥትን አዲስ የኅሊና ውቅር (Mindset)እና የአመራር ዘይቤ ይጠይቃል። ኢኖቬሽንን መደገፍ ማለት  ያልታወቀ ጉዳይን እንደ መቀበል ነው፡፡ መንግሥት የመጪ ጊዜና እየገነኑ ለመጡ ቴክሎጂዎች መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ  እንዲሁም ብርቱ፣ ልዩ ፈጠራ ላላቸውና ቁርጠኛ ለሆኑ ግለሰቦች  አዳዲስ ቢዝነሶችንና አገልግሎቶች እንዲጀምሩ፤ ሥራዎችን እንዲፈጥሩ የሚረዳ አስቻይ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡

እንደ እኛ ላሉት በማደግ ላይ ላሉ ኢኮኖሚዎች የሳይበር ደኅንነት ፣ ጎጂ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት፣ በሀብታሞች እና በድኻዎች መካከል እያደገ የመጣው ክፍተት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በብቃት ለመጠቀም ያለመቻል ተጠቃሽ ስጋቶች ናቸው። ለምሳሌ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን ግለሰቦችን ለመከታተል እና ለማግኘት፣ የክትባት ምርምር ለማመቻቸት ፣ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ውድቀትን ለመታደግ ሰዎች በርቀት እንዲሠሩ በመርዳት የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ጠቀሜታ ላይ ጠንካራ ትምህርቶችን ለመውሰድ አስችሏል። 

ዞሮ ዞሮ ትልቁ ፈተና  የዲጂታል መገለጫን ወይም ምንነት ሙሉ በሙሉ ለመረዳትና ለማሰስ የሚታየው ቸልተኝነት ነው። እንዲሁም ከሥርዓተ ጾታ፣ ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና በዋዛ እንዳይታለፉ  በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስጋት ተጋፋጭነትና  የባለቤትነት ስሜት  አስፈላጊ ነው።  

አዳዲስ ዕድሎችን ሙሉ በሙሉ ተገንዝቦ ለመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ውጭ ካሉት መማርን ፣ ትብብርን እና አጋርነትን ይጠይቃል ። ይህ ስትራቴጂ የበለጸገው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ፣ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ መሪዎች ጋር በተደረገ ትብብር ነው። በተለይም ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፣ ለኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፓዝ ዌይ ፎር ፕሮስፐሪቲ ኮሚሽን፣ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፣ ቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት፣ ዳልበርግ እና ለተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ልዩ ምስጋና ይድረሳችው።  አንዳችን ከሌላው መማርን እንቀጥላለን ፣ በጥልቀት አብረን እንሠራለን ፣ እናም የበለጠ ጠንካራ እና በርካታ የፈጠራ አጋርነትን እናጠናክራለን።

ይህ ስትራቴጂ የመጀመሪያ ርምጃ እና የድርጊት ጥሪ ነው። ድርጊት ሕይወት ይዘራል፤ ዜጎች የሚገባቸውን የብልጽግና ሕይወት በማሳካት ሂደት ትርጉም ያለው ውጤትም ይሰጣል ። ይህ ስትራቴጂ የመጀመሪያው ርምጃ እና በመሠረታዊነት ወደ ድርጊት የሚያመራ ጥሪ ነው ። ለኢትዮጵያ የብልጽግና ተስፋ መሳካት ቃል የገቡት ሁሉ በመተጋገዝ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንዲያበረክቱ ጥሪዬን አቀርባላሁ። አብረን እንደምናሳካውም ሙሉ እምነት አለኝ።

ዐቢይ አሕመድ አሊ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ