በኢትዮጵያ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ ከሆነው የግብርና ዘርፍ ውስጥ የእንስሳት ሀብትን በቴክኖሎጂ ማዘመንን የተመለከተ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
አውደ ጥናቱ ሁሉንም የእንስሳት ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ባለድርሻ አካላትን በአንድነት ለማሰባሰብ ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ሂደት፣ መሰረታዊ ችግሮች መለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ያኒያ ሰይድመኪ (ፒ ኤች ዲ) ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ብዛት ቀዳሚ ብትሆንም ምርቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ባለመሆኑ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነች ተናግረዋል።
የእንስሳት ሀብትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከክልል መንግስታት፣ በየክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በየአካባቢው ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር የወተትና የስጋ ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት ሃብት ልማት ፕሮጀክት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በሶማሌ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን የደረሱበትን ደረጃ በማቅረብ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል።