የአለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት አጋዥ የሆነው “ወደ አዲስ ጉዞ” የተሰኘው ተከታታይ ዝግጅት አካል “የዲጂታል አካታችነት” ላይ ያተኮረው ውይይት በበይነ መረብ ተካሂዷል።
መድረኩን የከፈቱት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካታች ማደረግ ላይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ፈተናዎች የተደቀኑበት ነው ብለዋል።
የአለማችን ክፍል ግማሹ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንኙነት ውጪ መሆኑ ያሳዝናል ያሉት ፕሬዝዳንቷ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሁሉንም አካታችና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ሀገራት አበክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የዲጂታል አካታችነትን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጡት ፕሬዝዳንቷ ይህንን እውን ለማድረግ የብሄራዊ የቴሌኮሙኒኬሽን ተቆጣጣሪና የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን መቋቋሙን አንስተዋል።
የዝግጅቱ ዋና ትኩረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አካታችነት ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችንና አቅም የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘርፉ እኩል ተጠቃሚ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው።
ወደ አዲስ ጉዞ በሚል የዲጂታል አካታችነት ላይ በተደረገው ውይይት የተለያዩ ሀገራት የመንግስት ኃላፊዎች፣ የአለም አቀፍ ድርጅት መስራቾችና ኃልፊዎ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
አለም አቀፉ የቴሌኮም ልማት ኮንፈረንስ በቀጣይ አመት በኢትዮጵያ የሚደረግ ሲሆን የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ነው።