የዲጂታል ቴክኖሎጂ

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ማለት የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን፣ መተግበሪያዎችንና የበይነ-መረብ ግንኙነትን በመጠቀም ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ፣ በቀላሉና በፍጥነት የመከወን አሰራር ማለት ነው፡፡ በርቀትና በጊዜ ሳይገደብ እጅግ በርካታ መረጃዎችን በአንድ ቦታ ማግኘት፣ ብዙ ስራዎችን በእጭር ጊዜ መከወን፣ ግብይቶችን በአካል መሄድ ሳያስፈልግ መፈፀም፣ እቃዎችን ባሉበት መረከብ፣  የመንግስት አገልግሎቶችን ባሉበት ሆኖ ማግኘትን ያካትታል፡፡ በአንድ ማዕከል የተከማቸን መረጃ በሁሉም የዓለም ጫፍ ማግኘት ማለት ነው፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ በማዘመንና በማሻሻል ብዙ ገፅታዎችን ቀይሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ባልተገመተ መልኩ ለውጥ ካመጡ መስኮች መካከል ቱሪዝም፣ ስራ፣ ግብይት፣ መዝናኛ እና ግንኙነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡  መረጃን እንኳ መጥቀስ ብንችል በዚህ ቅፅበት በዓለም ጫፍ የተፈጠረን ክስተት በዚያው ቅፅበት፣ በፎቶ፣ በድምፅ፣ በተንቀሳቃሽ ምስል እና በፅሁፍ ማግኘት የሚቻልበት ስርዓት ተፈጥሯል፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጥቅሞች

1. ማህበራዊ ግንኙነት

የዲጂታል ቴክኖሎጂ በአቅራቢያቸው ሰው የሌላቸው ሰዎችን ከብቸኝነት ገላግሏቸዋል፡፡ አንድ ሰው ከየትኛውም የዓለም ጥግ ያሉ ቤተሰቦቹን፣ ዘመዶቹን አልያም ወዳጆቹን በቀላሉ በበይነ መረብ ግንኙነትና በተለያዩ መተግሪያዎች ሊያገኛቸው ይችላል፡፡ ግንኙነቱ በፅሁፍ፣ በምስል፣ በድምፅና በተንቀሳቃሽ ምስል ሊሆን ይችላል፡፡ ድረ-ገፅ፣ መተግበሪያ፣ ሶፍትዌር፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ ላፕቶፕና ሞባይል በዲጂታል ዓለም ውስጥ ሰዎችን ከብቸኝነት ገላግለዋል፡፡ ግንኙነትንም ወደ ቅፅበት ቀይረዋል፡፡ ሰዎች ኑሯቸውን፣ ወሏቸውን፣ ስሜታቸውን ሁሉ በሚፈልጉት አግባብ ለሌሎች ማድረስ የሚችሉበት፣ እነሱም የሚቀበልቡት መድረክ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ግንኙነት የሰዎችን የዲጂታል ማህበራዊ ግንኙነት አሳድጎታል፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰዎች በአካል የሚደረግ ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ጥላ ማጥላቱ ግን አልቀረም፡፡ ሩቅ ካሉ ሰዎች ጋር ረዘም ላል ጊዜ በፅሁፍ ማውራትን መምረጣቸው እርስ በእርስ ያለ የአካል ግንኙነትን ቀንሷል፡፡ ሰዎች በቤተሰብ መካከል ያለን ቅርርብ እያላላው ነው፡፡ እንደዚህ አይነት አሉታዊ ትፅዕኖዎችን መፍትሄ ማበጀት ግን ይጠይል፡፡

2. ፈጣን ግንኙነት

የበይነ መረብ ግንኙነት ቀድሞ ከነበረበት በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ ፈጣን የበይነመረብ ግንኙነት በቅፅበት ትላልቅ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን፣ የድምፅ ቅጂዎችን፣ የመረጃ ሰነዶችን በየትኛውም የዓለም ጥግ ላለ ሰው ወይንም ሰዎች በፍጥነት ለመላክ የሚያስችል ደረጃ ላይ አድርሷል፡፡ ይህ የመረጃ ልውውጥ ቀድሞ ረዘም ያለ ጊዜን ይፈጅ ነበር፡፡

3. ሁለገብ ሥራ ለመስራት

የሥራ ባህሪ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተለውጧል ፡፡  የተለያዩ የግንኙነት አማራጮችን በመጠቀም ብዙ ሰዎች ስራዎችን ቤታቸው ሆነው መከወን የሚያስችላቸው እድል ተፈጥሯል፡፡  ይህ አይነቱ ስራ ሰዎች በርቀት ሳይገደቡና ወደ ስራው መሄድ ሳያፈልጋቸው ስራው ወደ ቤታቸው የሚመጣበት አሰራር ነው፡፡ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ስራዎችን እንዲሰሩም አድል ፈጥሮላቸዋል፡፡

4. የትምህርት እድሎች

እሁን የበይነመረብን ግንኙነት ያለው ማንኛውም ሰው በዓለም ላይ በመረጃ ድር ከተሳሰረው መረጃ ያልተናነሰ እውቀትን መጨበጥ ይችላል፡፡  ከዓለም ህዝብ ጋር በቀላሉ በመገናኘት በቀጥታ ከምንጮች መማር ይችላለ ማለት ነው፡፡ በባሉበት (ኦንላይን) የሚሰጡ ትምህርቶችን በመከታተል የትኛውንም እውቀት የመጨበጥ እድል በማንኛውም የበይነ መረብ ግንኙነት ተጠቃሚ ሰው እጅ ላይ አለ፡፡ ይህ እድል የአካል ጉዳት ካለባቸው ሰዎች ጀምሮ ትምህርት ቤት ከፍሎ ለመማር አቅም እስከሚያንሳቸው ሰዎች ድረስ እኩል ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

5. ቅመራ* (አውቶሜሽን)

ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽኖችን የበለጠ የዘመኑ እያደረጋቸው ነው፡፡ ማሽኖች ከሰው ንክኪ ውጭ በሆነ መልኩ ስራቸውን እንዲከውኑ እያስቻላቸው ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በድግግሞሽ ምክንያት ለሰዎች አሰልቺ የሆኑ ስራዎችን በቅመራ (አውቶሜሽ) ማሽኑ ራሱ እንዲሰራቸው ማድረግ ችሏል፡፡ ይህም ሰራተኞችን የቅመራ ስራውን መስራት (አውቶሜት ማድረግ) ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ በማድረግ ስራቸውን ማቃለል ችሏል፡፡ በማሽን ስለሚሰሩ ምርቶች በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጡ በማድረግ ለተጠቃሚዎችም የዋጋ ምቹነት መፍጠር ችለዋል፡፡

6. የመረጃ ማከማቻ

ዲጂታል ቴክኖሎጂ በአንጻራዊንት በአነስተኛ ቦታዎች ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ መረጃዎችን ለማከማቸት ያስችለዋል።  ፎቶዎችን ፣ ሙዚቃዎችን ፣ ቪዲዮዎችችን ፣ የሰው መረጃ እና ሌሎች ሰነዶችን እንደ ሞባይል ስልኮች ባሉ ትናንሽ መሣሪያዎች መያዝ አስችሏል፡፡  እንዲሁም እነዚህ መረጃዎች በዳመና ማስላት  ኦንላይን ለታሰሱ በሚችል መልኩ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡  ይህም የበይነመረብ ግንኙነት ያለው ማንኛውም ሰው ባለበት ሆኖ እንዲጠቀምባቸው እድል ይሰጠዋል፡፡

7. አርትዖት

ዲጂታል ቴክኖሎጂ የፅሁፍ እና የተንቀሳቃሽ ምስል መረጃዎችን የማስተካክያ ስራ ለመስራት ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው፡፡ ቀድሞ በትላልቅ ስቱዲዮ በውድ ዋጋ የአርትኦት ስራ ይሰራላቸው የነበሩ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች አሁን ቤት ውስጥ በስልክና በኮምፒውተር በቀላሉ መሰራት ተችሏል፡፡ ፎቶ የማሳደግ፣ ቀለም የመቀየር፣ የመቁረጥና የመሳሰሉት ስራዎች በቀላሉ መሰራት ችለዋል፡፡

8. ትክክለኛ ቅጂ

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ካሉት ታላላቅ ጥቅሞች አንዱ ማንኛውንም መረጃ ትክክለኛ ቅጂ ለማድረግ እድል መስጠቱ ነው፡፡ ፡፡ ለምሳሌ የሥራ ሪፖርትን መጻፍ እና ለብዙ ተቀባዮች በኢሜል መላክ ወይም ብዙ የፎቶ ቅጂዎችን ለቤተሰብ እና ለጓደኞች ማሰራጨት ተችሏል ፡፡ የቁስ ቅጂም (3ዲ)  ዘርፉን በእጅጉ እያዘመነው ይገኛል፡፡

9. ጂፒኤስ እና ካርታ

ቀድሞ አካባቢን ለማወቅ የወረቀት ካርታ ማመላከቻን መጠቀም የተለመደ ነበር፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግን አሁን ነገሮችን ቀይሯቸዋል፡፡ ከሳተላይት መረጃዎች በመሰብሰብ የሚሰራው የአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂ ፒ ኤስ) አሁናዊ መረጃዎችን በበይነ መረብ ግንኙነት ያደርሳል፡፡ አሁን ያለንበትን ቦታ፣ መድረስ የምንፈልግበትን ቦታ፣ የሚወስድብንን ሰዓት፣ የመንገዱ የመዘጋጋትና ነፃ የመሆን ሁኔታ፣ መዘጋቱንና መከፈቱን፣ አማራጭ መንገዶችን በአሁናዊ መረጃ ያሳውቀናል፡፡ የተከፈተ ነዳጅ ማደያ ወይም የመድኃኒት መደብር ማግኘት ከፈለግንም ነገሩ ቀላል ሆኗል፡፡

10. መጓጓዣ

ባቡሮች እና አውሮፕላኖች የዲጂታል ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ፡፡  የህዝብ ማመላለሻና  እና የጭነት መኪናዎች መዳረሻቸውን እጃችን ላይ ባለ መሳሪያ ማወቅ እንችላለን፡፡ የአውሮፕላንና የባቡር ትኬት ለማግኘት፣  ፓስፖርት ለማውጣት፣  በጉምሩክ የመመርመር እና የማለፍ ሂደትን ለማፋጠን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ከፍ ሲልም ሰው አልባ አውሮፕላኖችንና ባቡሮችን ጥቅም ላይ ለማዋልም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡

11. ዝቅተኛ ዋጋ

ለኢንተርኔት አገልግሎት ከመክፈል እና ለመጠቀሚያ መሳሪዎች ከሚወጣው ወጪ በስተቀር  በዲጂታል ዓለም ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ነፃ ናቸው፡፡ ኢሜል መላላክ ፣ ከቤተሰብ ጋር በቪዲዮ መገናኘት፣ በይነ መረብ  በሚጠቀሙ መተግበሪያዎች መደዋወል፣ መረጃዎችን መጠቀም የመሳሉት በነፃ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዝቅተኛ ወጪ ራስን ማስተማር ፣ የንግድ ሥራ መስራት ፣ ዕቃዎችን መግዛትና መሸጥ ወይም በመስመር ላይ ገንዘብ ማግኘት ዕድሎችን እያስገኘ ነው ፡፡

12. መዝናኛ

አብዛኛው የመዝናኛ ኢንዱስትሪ እና ሰዎች እራሳቸውን የሚያዝናኑበት መንገድ ከበይነመረቡ አብዮት ጋር ተያዞ በእጅጉ ተቀይሯል፡፡ ብዙ ሰዎች በባሉበት (ኦንላይን) በማህበራዊ መገናኛ በዙሃን ይዝናናሉ፡፡   በኮምፒዩተርና ተንቀሳቃሽ ስልክ ጨዋታዎች በመጫወት ደስታቸውን ያገኛሉ ፡፡ የቴሌቪዥኖች እና የሬዲዮ የመዝናኛ ስርጭቶችን፣ ፊልሞችንና ድራማዎችን፣ ሙዚቃዎችን  በበይነ መረብ ግንኙነት በዲጂታል መንገድ ማግኘት ተችሏል፡፡

13. ዜና

እንደ ጋዜጣና መፅሄት ያሉ የህትመት ውጤቶች ባልተገመተ መልኩ አንባቢ እየቀነሰባቸው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች አሁን ዜናዎችን እና መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ፣  በድረ-ገፅና በይነ መረብን በሚጠቀሙ ማሰራጫዎች ቀጥታ ዜናዎች ማግኘት ችለዋል፡፡ ቴሌቭዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ሳይቀሩ ዲጂታል ሆነዋል፡፡ ስርጭቶቻቸውን ከሬዲዮና ቴሌቭዥን በተጨማሪ በይነ መረብን በመጠቀም ማስተላፍ ጀምረዋል፡፡

ከመደበኛው መገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ ሰዎችም የመረጃ ምንጭ የሖኑበት ከባቢያዊ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አንድ ሰው የእጅ ስልኩን ተጠቅሞ ፎቶዎችን በማንሳት፣ ተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረፅ በአካባቢው ስለተፈፀመ ክስተት በዓለም ጥግ ላሉ ሰዎች ሁሉ መረጃውን በቅጽበት ማድረስ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጠሯል፡፡ በዚህ መሰረት ግልሰቦችም ጭምር የዜና ምንጭ ሆነዋል፡፡

ነገር ግን ግለሰቦች አርታኢ ስለሌላቸው የውሸት መረጃዎችን ለመልቀቅ እድሉ ስላላቸው እንደዚህ አይነት ሃሰተኛ መረጃዎችን የምንቆጣጠርባቸው ስርዓቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡

14. ጦርነት

የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ወታደሮች በአካል በጦር ሜዳ ተግኝተው መዋጋት እንደማይጠበቅባቸው እያሳየ ነው፡፡ ጦርነቶች ሁሉ የሰዎችን ጉዳት ባስቀረ ምልኩ በማዕከል ባለ የቁጥጥር ጣቢያ መካሄድ ጀምሯል፡፡ ሰው አልባ አውሮፕላኖችንና ሚሳኤልን በመጠቀም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተፈለገውን ኢላማ ማሳካት ይቻላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በዲጂታ ቴክኖሎጂ የበይነመረብ ግንኙነትና ጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

15. ባንክ እና ፋይናንስ

ዲጂታላይዜሽን በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ውስጥ ትልቅ አብዮት ማምጣት ችሏል፡፡  የባሉበት (ኦንላይን) ባንኪንግ አገልግሎት ሰዎች ባሉበት ሆነው መተግሪያዎችን በመጠቀም በስልካቸው ወይም በኮምፒውተራቸው ገንዘብ ማንቀሳቀስ  ችለዋል፡፡ ያላቸውን ገንዘብ ማወቅ፣ ገንዝብ ማስተላለፍ፣ እቃ መግዛትና መሸጥ፣ ክፍያ መፈፀም አስችሏቸዋል፡፡

ከባንክ ውጭ ፣ እንደ አክሲዮን መግዛትና መሸጥ ያሉ ሌሎች የገንዘብ ጉዳዮች በባሉበት (ኦንላይን) ላይ ማስተናገድ ተችሏል። በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገንዘብ ማስተላለፍም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የፈጠራ ሥራ ታይቷል ፡፡

16. አነስተኛ መጠን ያላቸው መሣሪያዎች

የዲጂታል ቴክኖሎጂ የመጠቀሚያ እቃዎችን ለአያያዝ ምቹ ማድረግን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ እሁን በአካባቢያችን የምንይዛቸው ስልኮችንና ትናንሽ-ኮምፒውተሮች ናቸው ፡፡ እነዚህ በእጃችን የምንይዛቸው መሳሪዎች የበይነመረብ አሰሳ ማከናወን፣ የሂሳብ ስሌት መስራት ፣ ጉዞዎችን ማቀድ ፣  ፎቶግራፎችን ማንሳት እና መጫወት ፣  ድምፅና እና ቪዲዮዎችን መጫወት ፣ ስልክ ማውራት የመሳሰሉ ተግባራትን እንደናከናውን ያስችሉናል፡፡  የንግድ ስራ ለመስራት፣ የገንዘብ ልውውጥ ለማድረግ፣ መረጃ ለማስተላለፍ፣ አግልግሎቶችን ለማግኘት እያስቻሉን ነው፡፡

ምንጭ፡- turbofuture.com

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook