የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ለመተግብር የሚያስችል የ200ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ እና በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ተጠሪ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ፈርመውታል።

ገንዘቡ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለመደገፍ የሚውል ሲሆን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ለተቀረፁ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የተመደበ ነው።

ፕሮጀክቶቹ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና የሰላም ሚኒስቴር የሚመሯቸው ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የብድር ስምምነቱ ኢትዮጵያ አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የያዘችውን እቅድ እውን ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ተጠሪ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ብድሩ ለኢትዮጵያ እንደተሰጠ ጠቁመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) ኢትዮጵያ “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን” ቀርፃ ወደ ትግበራ መገባቱን ጠቁመዋል።

በስትራቴጂው የኢንተርኔት ግንኙነት፣ አስቻይ ሁኔታ፣ ዲጂታል አገልግሎት እንዲሁም ፖሊሲና ስትራቴጂ ቅድሚያ የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ይህ የብድር ስምምነት በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ ለተካተተው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን መሆን የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

ገንዘቡ በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ውስጥ ቅድሚያ የተሰጣቸውን ዘርፎች ለመተግበር ያስችላል ተብሏል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook