የተቋሙ ሰራተኞች የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸምና በመንግስት ሰራተኞች የድልድል መመሪያ ላይ ተወያይተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) ባለፉት ወራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ ምቹ የኢኖቬሽን ስነ ምህዳር መፍጠር፣ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
የተቀናጀ የኢንተርፕራይዝ ሃብትን የማስተዳደሪያ ስርዓት በሁሉም የፌዴራል ተቋማት አገልግሎት ላይ ለማዋል የታየው ጅምር ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። የኤሌክትሮኒክ ቢሮ አሰራር ላይ ተቋሙ ግንባር ቀደም ሆኖ በሁሉም የመንግስት ተቋማት ለማስተገበር እየሰራ ስለመሆኑ ያብራሩት ሚኒስትሩ ለስኬቱ ሰራተኛች በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በውይይቱ በትግበራ ሂደት ላይ የሚገኙትን የዳታ ማዕከል ግንባታ፣ የኤሌክትሮኒክ መንግስትን ለመተግበር የመሰረተልማት ማሻሻል፣ የመንግስት ፖርታሎችን ማልማትና ማሻሻል ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች መሆናቸው ተነስቷል።
የአስር ዓመቱን እቅድ ለማሳካት ያለመው አዲሱ የሰራተኛ ድልድል መመሪያ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ሰራተኛው የድልድል ኮሚቴም መርጧል። በተቋሙ ለአመታት የልተቋጩ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን ለስኬቱ ስራተኛው በትብብር መንፈስ እንዲሰራ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።