የዲጂታል ክህሎት ያለው ዜጋ ለመፍጠር ያስችላሉ የተባሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት በኢትዮጵያ ሊቋቋሙ ነው፡፡


በአፍሪካ ውስጥ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕከል እንዲሆኑ ከተመረጡ 8 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ተመርጣለች።

ማዕከላቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስልጠናዎችን ለማግኘትና የብቃት ማረጋገጫ ለመውሰድ የሚያገለግሉ ሲሆን ስራ መፍጠር የሚችልና ተወዳዳሪ የዲጂታል ክህሎት ያለው የሰው ሃይል ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ማዕከላቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ጋር በመተባበር የሚያቋቁሟቸው ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የሳይንስ ካፌዎችን እና የወጣት ማዕከላትንም በዚህ ውስጥ በማካተት ይሰራል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በመሰረታዊ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ የዲጂታል ክህሎት ለዜጎች መገንባት ለኢኮኖሚ ሆነ ለማህበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው ብለዋል፡፡

ሴቶች፣ በገጠሩ የሚኖረው የማህበረሰብ ክፍል እንዲሁም የአካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች ላይ በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ፣ የዲጂታል ክህሎት ክፍተትን ማጥበብና በዲጂታሉ አለም ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የአለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት የአፍሪካ ክልል ፅ/ቤት ኃላፊ አኒ ራቼል ኢነ አለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት በኢትየጵያ የዲጂታል ትራንስፊርሜሽን ማዕከላትን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ውስጥ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕከል እንዲሆኑ ከተመረጡ 8 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ሆና የተመረጠች ሲሆን ማዕከላቱን ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዝግጅቱ ላይ የፌደራል መንግስትና የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች እና የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

 

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook