የኢትዮጵያ የዲጂታል ጤና ስትራቴጂን ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ጋር በማጣጣም በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ባዩ (ፒ ኤች ዲ) እንደገለጹት የዲጂታል ጤና ዋና ዓላማ ጥራት ያለው፣ ፍትሃዊና በቴከኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው።
የዲጂታል ጤና ስትራቴጂው ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሰኬት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፣ ስትራቴጂውን መሰረት ያደረገ የቴከኖሎጂ አጠቃቀም ቴከኖሎጂው የሚሰጣቸውን የእድገት እና የመሻሻል እድሎች አማጦ ለመተግበር ያስችላል።
ከዚህም በላይ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሊመጡ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ቀድሞ በመለየት ለመቀነስ ያግዛልም ብለዋል።ሌሎች ዘርፎችም የጤና ጥበቃ ሚኒሰቴርን ልምድ እና ከአገራዊው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ የተቀዳ የየዘርፋቸውን ዝርዝር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ሊያውጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዲጂታል ጤና ስትራቴጂው ሰነድ የዘርፉ ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት እና የልማት አጋሮች በተገኙበት መስከረም 5/ 2014 ዓ.ም በተደረገ የውይይት መድረክ ወደስራ መግባቱ ይታወሳል።
በመድረኩ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና አይሲቲ ሃላፊዎች በዲጂታል ጤና ስትራቴጂ ሰነዱ ላይ ገለጻ አድርገዋል።