የዲጂታል ኢትዮጵያ የበይነ መረብ ውይይት አካል የሆነውና የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ መደግፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፏን ለማዘመንና የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየሰራች ትገኛለች፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነትን ማሳደግና ለማምረቻው ዘርፍ ግብዓት እንዲሆን ማድረግ ላይ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የዘርፉ ባለሙያዎች ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ግብርናው እንዲዘምን ለማድረግ የዲጂታል ግብርና ፕላትፎርም መገንባትና የግብርና ቴክኖሎጂ ስራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩትን መደገፍ እና ማበረታታት ላይ ይሰራል ብለዋል፡፡
የ‹‹ለርሻ›› መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አብረሃም እንድሪስ ለአርሶ አደሮች በአጭር የስልክ ቁጥር ጥሪ የግብርና መረጃዎችን በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን አቅም በመጠቀም የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ላይ መስራት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች የግርናውን ዘርፍ ለማዘመን፣ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ሰለሚሰጧቸው አገልግሎት፣ በዘርፉ ስላሉ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡