የጭነት አግልግሎትን ያቀላጥፋል የተባለ ዚትራክ የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ሆነ።

መተግበሪያው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ፒ ኤች ዲ) እና የ ዚ ትራክ የትራንስፖርት አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ዋና ስራ አስኪያጅ ዮዲት ደነቀው በተገኙበት ነው ይፋ የተደረገው።

መተግበሪያው ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን የለማ ሲሆን በስልክና ኮምፒውተር ላይ በመጫን የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማቀላላተፍ የሚያግዝ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) የኤሌክትሮኒክስ ንግድ በኢትዮጵያ በተሟላ ደረጃ ለመተግበር እንደ ዚትራክ ያሉ መተግበሪያዎች አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ችግሮች በአሰራር፣ በብቁ የሰው ሃይል፣ በአደረጃጀትና በቴክኖሎጂ መቅረፍ ከተቻለ ኢትዬጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ ሃብ ማድረግ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

በጭነት አገልግሎት ለተሰማሩ አስተላላፊዎች፣ አሸከርካሪዎችና ደንበኞች ስራዎቻቸውን ያቀላጥፋል የተባለው መተግበሪያው ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቅቋል ተብሏል።

ዚትራክ ሶስት መተግብሪያዎችን የያዘ ሲሆን እርስ በእርሳቸው የሚናበቡ የጭነት አገልግሎት ሰጪውንና ደንበኛውን የሚያገናኙ፣ ጭነቱ የደረሰበትን ቦታና የሚደርስበትን ጊዜ ለመከታተል የሚያስችሉ ናቸው። ስርዓቱ በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን አርቲስት ሰለሞን ቦጋለን አምባሳደር አድርጎ መርጧል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook