የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የክልሎችን የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ዝግጁነትን በተመለከተ ያደረገውን የደሰሳ ጥናት ለየክልሎቹ ባለድርሻዎች አቅርቧል።
የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ዝግጁነት የዳሰሳ ጥናት የተካሄደው አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳና አዳማ ከተማ አስተዳደሮችና ዩኒቨርሲቲዎች ነው።
በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት የተለዩ ክፍተቶችን በመሙላት ክልሎች የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን በተጠናከረ መልኩና በቅንጅት እንዲሰሩ ለማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እየተደረገ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሃመድ (ፒ ኤች ዲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ቁርጥኝነት መኖሩ የኢትዮጵያን የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ደረጃን ለማሻሻል በሚሰራው ስራ ውስጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ደረጃው ሲሻሻል አቅም ያላቸው ባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይህ ደግሞ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
የመንግስት አገልግሎትን ዲጂታል በማድረግ ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አንዱ አለም አቀፍ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ደረጃ መለኪያ መስፈርት ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አመታት የአለም አቀፍ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ደረጃዋን በማሻሻል ከ100ዎቹ ዝርዝር ውስጥ የመግባት እቅድ ይዛ እየሰራች ነው።