የከተሞች መረጃ አስተዳደር (ፖርታል) ከተሞች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የሚሰሩትን ስራ ህዝብ እንዲያውቅላቸው፣ የሚሰጡት አገልግሎት እንዲተዋወቅ፣ ከውጭ የሚመጡ ሰዎች የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አዳማ እና አርባምንጭ ከተሞች የከተማ መረጃ አስተዳደር (ፖርታል) እየለማላቸው ሲሆን ራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ለባለሙያዎቻቸው በስራ አመራር ኢንስቲቲዩት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

ስልጠናው ከተሞቹ የመረጃ አስተዳደሩን እንዲያስተዳድሩ፣ መረጃ እንዲያከማቹ፣ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እንዲጨምሩ፣ አጠቃቀሙን እንዲያውቁ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችላቸው ነው።
የከተማ የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) የከተማ ነዋሪዎችና ከከተማ ውጭ የሚኖሩ ሰዎች ስለ ከተሞች የሚፈልጉትን መረጃ ባሉበት ሆነው እንዲያገኙና የከተማዎቹ ነዋሪዎች መንግስት የሚሰጠውን አገልግሎት ባሉበት ሆነው እንዲያገኙም ያስችላል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ባዩ (ፒ ኤች ዲ) የከተማ መረጃ አስተዳደር ዜጎች በቂ መረጃ እንዲያገኙና ከተሞች እድገታቸው እንዲፋጠን ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በቀጣይ ሌሎች ከተሞችም የከተማ የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) እንዲኖራቸው እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ በየሁለት አመቱ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ የሚወጣ ሲሆን ይህ ስራም ኢትዮጵያ ያላትን ደረጃ ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎች አካል ነው።