ደመናን በማዝነብ ቴክኖሎጂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የውሃ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል:- ዶክተር አህመዲን መሐመድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ

ደመናን አበልፅጎ በማዝነብ ቴክኖሎጂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የውሃ መጠን እንዲጨምር መደረጉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ገለጹ።

የዘርፉ ባለሙያዎች ደመናን ማዝነብ የአየር ሁኔታን በሰው ሰራሽ መንገድ የመቀየር ቴክኖሎጂ አካል መሆኑን፤ ዓላማውም ከደመና የሚገኝ የዝናብ ዓይነትና መጠንን መለወጥ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቴክኖሎጂው በሁለት መንገዶች የሚካሄድ ሲሆን የዝናብ ማበልጸጊያ ንጥረ ነገርን ከደመና በላይና ከታች ሆኖ በአውሮፕላን በመርጨትና ከመሬት ሆኖ ንጥረ ነገሩ በጄኔሬተር አማካኝነት በመልቀቅ የሚከናወን መሆኑ ይገለጻል።

ኢትዮጵያ ደመናን በማልማት የማዝነብ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ባገኘችው ድጋፍ ስራውን ከጀመረች ሁለት ወራትን አስቆጥራለች።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዘርፉን ለማልማት ከ10 በላይ የመንግሥትና የግል ዘርፎችን በማቀናጀት ግብረ ኃይል አቋቁመዋል።

ቴክኖሎጂው ኢትዮጵያ ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የምትጠቀማቸው ግድቦች የውሃ መጠን እንዲጨምር በማድረግ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ኢዜአ የግብረ ኃይሉን አባላት አነጋግሯል።የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ደመና የሚፈጠረው የውሃ ትነትን መሰረት አድርጎ መሆኑን ይናገራሉ።

ወደ ሰማይ የሚሄደው የውሃ ትነት ክብደት ሲኖረውና የውሃ እንክብሎቹ አንድ ላይ ሲሆኑ ዝናብ ሆኖ የመውረድ አቅም እንደሚኖረውም ነው የተናገሩት።

የውሃ እንክብሎቹ ስስ በሚሆኑበትና የሳሳ የደመና ክምችት በሚኖርበት ጊዜ አቅምና ክብደት ስለማይኖራቸው ዝናብ ላይፈጠር እንደሚችል ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ደመናን በማልማት የማዝነብ ቴክኖሎጂ የሳሳውን የደመና ክምችት በማልማት ለዝናብ ዝግጁ እንዲሆኑ አድርጎ ወደ መሬት ማውረድ ነው ይላሉ።

ይህን ሀሳብ ከመጠንሰስ ጀምሮ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ገቢራዊ እንዲሆን በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው በመጥቀስ፤የዝናብ መጠንን በመጨመር በቂ ውሃ እንዲኖር በማድረግ ግብርናውን ውጤታማ ማድረግ ያስችላልም ብለዋል።በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች እንዲሞሉ በማድረግ የኤሌክትሪክ አቅም እንዲስፋፋና እንዳይቆራረጥ በማድረግም አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።ለአብነትም ቻይና፣ ብራዚልና ካናዳ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦቻቸውን እንደሚሞሉ ጠቅሰዋል።የጊቤ ሶስትና የተከዜ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚይዙት የውሃ መጠን እንዲጨምር መደረጉንም አስታውቀዋል።ቴክኖሎጂው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሕዝብ ቁጥራቸው እየጨመረ በሚሄድ አገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረውም በማውሳት፤ በኢትዮጵያ በጅማሮ ላይ ያለ ቢሆንም በቀጣይ እየሰፋ እንደሚሄድ አክለዋል።የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ወራት ደመናን በማበልጸግ ረገድ ውጤታማ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።ቴክኖሎጂውን በዝናብ አጠር አካባቢዎች በመጠቀምና በሌሎች የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎችን በማስፋት ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አብራርተዋል።የአገሪቷን የተለያየ የአየር ሁኔታ መሰረት የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት በማድረግ ግብርናን ምርታማ ለማድረግ እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።እንደ ዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት መረጃ ደመናን በማበልጸግ የማዝነብ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ረገድ 40 አገራት ይጠቀሳሉ።ከነዚህ መካከል አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ አሜሪካና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ይገኙበታል፤ ከአፍሪካም ደቡብ አፍሪካና ቡርኪና ፋሶ ተጠቃሽ ናቸው።ኢዜአ

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook