ዲጂታል ኢኮኖሚ ማለት በዋናነት በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እገዛ የሚገነባ ኢኮኖሚ ማለት ነው፡፡ ይህ በግለሰቦች ፣ በኩባንያዎች ፣ በኮምፒተሮች ና በበይነ መረብ ግንኙነት ወዘተ መካከል በኢንፎርሜሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ሲ.ቲ.) የታገዙ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ፣ ስርዓቶችን ፣ ግብይቶችን እና ግንኙነቶችን ያጠቃልላል፡፡የደመና ማስላት (cloud computing)፣ በይነመረብ ቁሶች (Internet of Things) እና የመረጃ መረብ ደህነንነት (Cyber Security) በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑና የዲጂታል ቴክሎጂውን የሚደግፉ ናቸው፡፡
የዲጂታል ኢኮኖሚ ጥቅሞች
ዛሬ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው፣ ከመደበኛ ቢሮዎች ፣ ከቤታቸው ወይም አልፎ አልፎ በተለያየ ቦታ ቡና እየጠጡ በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው ስራዎችን ይሰራሉ፡፡
የሚሰሩበት ቦታ ቢቀያየርም በአካል ተገኝተው ከሚሰሩበት ልምድ ጋር ተመሳሳይ የሖነ የበይነ መረብ ግንኙነት ማግኘትን ግን ይጠይቃል፡፡ ይህ በአለም አቀፍ ደረጃ እያደገ በመጣው ተለዋዋጭና ምናባዊ የበይነ-መረብ ግንኙነት ቀልጣፋ አስተዳደርን ይጠይቃል፡፡
ሌላው ቀርቶ በተለያየ ቦታና የጊዜ ልዩነት ለዜጎች መዳረስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡
ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጥቅሞች ውስጥ፡-
1ኛ የንግድ ሥራ ዕድሎችን ያስፋፋል፡- የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ዲጂታላዜሽ አዳዲስ፣ ትናንሽ ንግዶች እና ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ እድል ይሰጣል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎቶች ግዥና ስርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታ እንዲሳተፉ ያበረታታል፡፡
2ኛ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል፡- የዲጂታል ኢኮኖሚው ለሥራ አጦች የስራ እድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋፀኦ ያደርጋል፡፡ በበይነ-መረብ ላይ የተመሰረተ ዲጂታል ንግድን ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ በመፍጠር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡
3ኛ ቀልጣፋ አገልግሎት ለህዝብ ለመስጠት ያስችላል፡- ዓለም አቀፍ የበይነመረብ ሽፋንን ማሳደግና እና ጠንካራ የመረጃ እና የግንኙነት መሠረተ ልማት አውታሮችን መዘርጋት በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ለህዝብ የሚሰጡ አግልግሎቶች ጥራታቸውን ለማሻሻልና ለማቀላጠፍ ይረዳል፡፡
4ኛ ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅዖ ያደርጋል፡– በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት ምክንያት በፈጠራ የታገዘ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ ይህ ለውጥ በሌሎች የኢኮኖሚው ዘርፎች ላይ የተወሰነ ጫና ማሳደሩ ግን አልቀረም ፡፡
5ኛ የኤሌክትሮኒክስ ንግድን ያስፋፋል፡- ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢ-ኮሜርስ ግብይቶች በፍጥነት መጨመራቸው ተመዝግቧል፡፡ ዲጂታይዜሽን ምርትና አግልግሎትን በተቀላጠፈ መልኩ ለመግዛትና ለማሰራጨት በጣም ቀላል፣ ቀልጣፋና ተመጣጣኝ ዋጋን በመፍጠሩ የተነሳ ሰዎች ኤሌክትሮኒክስ ንግድን በመምረጣቸው ዘርፉ እንዲስፋፋ ሆኗል፡፡
6ኛ የሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዲጂታል ስርጭትን ይፈጥራል፡- ዕቃዎች እና አገልግሎቶች የሚሰራጩበት መንገድ በዲጂታላይዜሽን በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል፡፡ አንድ ሰው ከአቪዬሽን እስከ ባንኪንግ ፣ ከመዝናኛ እስከ ትምህርት እና ኢንሹራንስ እንዲሁም ሆቴል ትዕዛዝ ድረስ ባለበት የሚፈልገውን ምርትና እና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ማግኘት ይችላል ፡፡
7ኛ ግልፅነት፡- ትላልቅ የንግድ ግብይቶች በዘመናዊው ኢኮኖሚ ውስጥ በመስመር (ኦንላይን) ላይ ይፈፀማሉ፡፡ ይህ የገንዘብ ዝውውር የወረቀት ገንዘብን ለማስቀርት የሚረዳ ሲሆን፣ ተጠያቂነትን በማስፈን የሚፈፀም ሙስናን ይቀንሳል፡፡
ተግዳሮቶች
ዲጂታል ኢኮኖሚ በባህላዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ብዙ ድርጅቶች ከንግድ ስርዓቱ ውጭ የማድረጉ ጉዳይ በፍጥነት እየጨመረ ነው፡፡ እንዲሁም ገዥዎች በእጅጉ ይፈልጉት የነበረውን አካላዊ ግብይት በማስቀረት በሻጮች እና በገዢዎች መካከል አካላዊ ግንኙነትን አሳጥቷል፡፡ አንዳንድ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉድለቶች፡-
1ኛ የሥራ ገበያ መቋረጥ፡- የጉልበትና የእጅ ስራን የሚጠይቁ ሂደቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂው በተለይም በቅመራ (ኦቶሜሽን) እና ዲጂታዜሽን ይተካቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሰራተኛ ቅነሳን በማስከተል የገቢ ልዩነቶችን ያሰፋል፡፡
2ኛ የመረጃ መረብ ደህንነት፡- በኢኮኖሚው ውስጥ ዲጂታላይዜሽን እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመረጃ መረብ ጥቃትና ምንተፋ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህንንም ጠንካራ የምስጠራ (cryptography) ሰራ በመሰራት የተረጋጋና ታዕማኒ የመረጃ መረብ ጥበቃን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
3ኛ ጠንካራ የመሠረተ ልማት መፈለጉ፡- ዘርፉ በኢንተርኔት፣ በቴሌኮሙኒኬሽንናና በሞባይል ዘርፎች ጠንካራ መሠረተ ልማትን ይፈልጋል ፡፡ የዲጂታል ግንኙነት ለመፍጠርና ከተሞችንም ሆነ መንደሮችን ለማገናኘት ጠንካራ የመሰረተ ልማት ግንባታ ይጠይቃል፡፡
ዲጂታይዜሽን ሰዎች መረጃዎችን ፣ ሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን በቀላሉ እና በፍጥነት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ እየተፈጠሩ ያሉ ምቹ ሁኔታዎች በዲጂታል መንገድ የሚፈፀም የገንዘብ ዝውውር እንዲጨምር አድርጓል፡፡ባለፉት 15 አማታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ምጣኔ ሀብቱ 11.5 ትሪሊዮን ዶላር ያስመዘገበ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ምርት 15.5 በመቶውን ይይዛል፡፡