የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች ከወከሉ አምባሳደሮችና የቆንስላ ጄኔራሎች ጋር በቴክኖሎጂ ዘርፍ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ሃብት በማፈላለግ፣ በዘርፉ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብና ተያያዥነት ባላቸው ዘርፎች ዲፕሎማቶች የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን አገር በቀል ምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ትግበራን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የያዘችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ከአገራዊ የምጣኔ ሃብት እድገትና ፍላጎት በመነሳት ማፈላለግና ማቅረብ የዲፕሎማሲ ሥራ ተልዕኮ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ እምየ ቢተው ኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያጸደቀቻቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ለዓለም ማሳወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘርፉ ሥራ በመፍጠር፣ ገቢ በማመንጨትና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ያለውን ፋይዳ በመረዳት አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ አገር ማምጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ፣ የዘርፉ ዐሥር ዓመት እቅድና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለዲፕሎማቶቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
በዘርፉ የዲፕሎማቶች ሚና ምን መሆን እንዳለበትም ተብራርቷል፡፡