ፖላንድ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እደግፋለሁ አለች።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከፖላንድ አምባሳደር ሚስተር ፕሪዝሚይስላው ቦባክ ጋር ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ዙሪያ መክረዋል።

ሚኒስትሩ ፖላንድ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላት ሃገር በመሆኗ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ከፖላንድ ልምድና ድጋፍ ማግኘት ትፈልጋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራች ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ፖላንድ በተለይ በኤሌክትሮኒክ መንግስት እና ኤሌክትሮኒክ ባንኪንግ ያላትን የዳበረ ልምድ መውሰድ እንፈልጋለን ብለዋል።

አምባሳደር ፕሪዝሚይስላው ቦባክ በበኩላቸው ሀገራቸው በኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ፣ በታክስ አስተዳደር፣ በዴታ ኢንተግሬሽን፣ በጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ሲስተም ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስራ ፖላንድ ለመደገፍ ዝግጁ ናት ያሉት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች በዘርፉ ልምድ የሚወስዱባቸውን እድሎችም እናመቻቻለን ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስራ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የትብብር ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ ስራ ለመግባትም ከስምምነት ደርሰዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook