በከተሞች እያደገ የመጣውን የህዝብ ቁጥር የሚመጠን አገልግሎት ለመሰጠት በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “ዘመናዊ ከተማ” (Smart City) ላይ ትኩረቱን ያደረገ የመሰመር ላይ ውይይት ተካሂዷል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በከተሞች እያደገ የመጣውን የህዝብ ቁጥር የሚመጠን አገልግሎት ለመሰጠት በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን መተግበር እና ዘመናዊ ከተማን መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።

መሰረተልማቶችን ለማስተዳደር፣ የትራፊክ ፍሰትንና የትራንስፖርት ስርዓትን ለማቀላጠፍ፣ ወንጀል ለመከላከል እና ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ለማድረግ መንግስት ጥረት እያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለስኬቱ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ወሳኘነት አለው ብለዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ምርምር ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ሰላምይሁን አደፍርስ በአካላዊው እና በዲጂታል አለም ውስጥ ያለውን የአስተሳሰብ ተቃርኖ የሚያስታርቅ የእይታ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።

ከተሞችን በቴክኖሎጂ የተገነቡ ማድረግ እና አገልግሎቶችን በዲጂታል አሰራር በመደገፍ ዜጎች ዘመናዊ ኑሮን መምራት እንዲችሉ ማድረግ ይገባል ተብሏል።

በውይይቱ በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ መሰረተ ልማት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ በውሃና ኤሌክትሪክ አግልግሎት ማዘመን ላይ ያሉ ዘመናዊ አሰራሮች እና ተሞክሮዎች ቀርበዋል።

በዘመናዊ ከተማ ግንባታ ውስጥ ገጠር የሚኖረውን ማህበረሰብ ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች መሰራት እንደሚገባም ተነስቷል። በቴክኖሎጂ የተገነባ ዘማናዊ ከተማ ውስጥ የሚጠራቀሙ መረጃዎች በቀጣይ ለሚወጡ ፖሊሲዎች እና ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ትልቅ ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ ተብሏል።

በውይይቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook