በጦርነቱ ውድመትና ዘረፋ የደረሰበትን የአቡነ ዮሴፍ ተራራ የአስትሮኖሚ (የሕዋ ምርምር) ጣቢያ ፕሮጅክትን መልሶ ለመገንባት እየተሰራ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት ሥራ አመራሮችን ያካተተ ቡድን በአቡነ ዮሴፍ ተራራ የሚገኘውን የሕዋ አካላት መመልከቻና ምርምር ጣቢያ ጎብኝተዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ከባህር ጠለል በላይ ከመሬት 4,280 ሜትር በላይ የሚገኘውን የምርምር ጣቢያው ፕሮጀክት በጦርነቱ ውድመትና ዘረፋ ደርሶበታል።

የተመራማሪዎች መኖሪያ ቤቶች፣ የሳተላይት መረጃ መቀበያ፣ የኢንተርኔት አገልጎሎት መስጫና የሕዋ አካላት መመልከቻ መሳሪያዎች ዘረፋና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል።

እንደ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር በለጠ፥ የአስትሮኖሚክስ (የምርምር) ጣቢያው ሀገራችን በስፔስና አስትሮኖሚክስ ዘርፍ እውቀት በማሸጋገርና የስፔስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።

በተጨማሪም አካባቢው በዘርፉ የዓለም አቀፍ ትኩረትን ስለሚስብ በእድገታችን ላይ ከፍተኛ አስተዋፆ የሚያደርግም ነው፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የሕዋ ምርምር ዘርፍ በአሁን ወቅት የሀገር ህልውናን ለማረጋግጥ ትልቅ የሆነ አቅም ያለው ሀብት ነው። በመሆኑም ጣቢያውን ሁሉም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ በአጭር ጊዜ መልሶ በመገንባት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪና የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ህብረት ም/ፕሬዝዳንት ሰለሞን በላይ (ፒ ኤች ዲ) በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የአስትሮኖሚካል ሳይቱ የተጀመረው በስፔስ ሳይንስ ማህበር ቢሆንም በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉበት ነው።

ይህ ፕሮጄክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕዋን በጥራት ለመመልከት ተመራጭ ከሆኑ ቦታዎች በተቀዳሚ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች አንዱ ነው። ጣቢያው ዓለም አቀፍ ሳይንቲፊክ ሱፐርቪዥን ቡድን ክትትል የሚያደርግበትና ከኢትዮጵያም አልፎ በሁሉም ዓለማት ተመራጭ በመሆኑ ፕሮጀክቱን ለማገዝ ሁሉም አካል እንዲረባረብ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook