የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር “የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ 2025” ፀድቆ ወደ ስራ ከገባበት ጀምሮ የተሰሩ ስራዎችና በቀጣይ ሊሰሩ በሚገባቸው ስራዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት፣ ከግሉ ዘርፍና ከስራ ፈጣሪዎች ጋር በአዲስ አበባ መክሯል።
ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን መሆን ተቋማት በትብብር እንዲሰሩና እንዲመክሩ ማስቻልን ታሳቢ ተደርጎ በተዘጋጀው በዚህ ዝግጅት ላይ በዘርፉ ተቋማት በተናጠልና በቅንጅት የሰሯቸው ስራዎች ቀርበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ምቹ የዲጂታል ከባቢ ሁኔታን በመፍጠር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
ምቹ የኢኖቬሽን ስነምህዳር መፍጠር፣ ለስራ ፈጣሪዎች አሰሪ ከባቢ ሁኔታን ማመቻቸት እና የተዋጣ ቴክኖሎጂን መጠቀም ላይ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በዝግጅቱ ላይ የቴሌኮም ሌብራላይዜሽን፣ የመረጃ መረብ ደህንነት፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ መሰረተ ልማት፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎ፣ ኢንደስትሪ፣ የህዋ ሳይንስ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ኢኮሜርስና ሌሎች ጉዳዮች ላይም የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ገለፃ አድርገዋል።
በዝግጅቱ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾችና ስራ ፈጣሪዎችን ጨምሮ የ16 ተቋማት ኃላፊዎች በዘርፉ የሰራቸውን ስራዎች አቅርበዋል።