ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው:- ሁሪያ አሊ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ

የ 2021 የአፍሪካ ቴክ ፌስቲቫል በበይነ መረብ እየተካሄደ ነው።

“በቴክኖሎጂ ሃያል ለመሆን የኢትዮጵያ ጉዞ” በሚል በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደ ፊት ለመራመድ እንድትችል እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎችን ለመድረኩ አብራርተዋል።

የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያ፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ፣ የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች አዋጅ፣ የግል ዴታ ጥበቃ አዋጅ፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የስራ ቅልጥፍናና የ ኢ-ክፍያ ስትራቴጂ የኢትዮጵያ መንግስት በትኩረት እየሰራቸው ያሉ ስራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዳረሻ ለማድረግ እየሰራን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለዚህ ስኬትም ምቹ የቴክኖሎጂ ከባቢ ሁኔታን መፍጠር ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

የአይሲቲ ፓርኮችን መሰረተ ልማት ማሟላት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ማስፋፋት፣ የዲጂታል እውቀትን ማስፋት፣ የበይነ መረብ ደህንነትን ማስጠበቅ እና የሰው ሃይል ግንባታ ላይ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች።

ከጥቅምት 29/2014 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው በዚህ የበይነ መረብ አውደ ርዕይ ከ300 በላይ ባለ ራዕዮች ንግግር ያደርጋሉ።

በመድረኩ ከተለያዩ የፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች አመራሮች፣ የቴክኖሎጁ የፋይናንስ ተቋማትና የባንክ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook