ኢትዮጵያ እና ራሺያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የነበሯቸውን ትብብሮች እና ውሎች በአዲስ የትግበራ ምዕራፍ ለማስቀጠል ተስማሙ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ የራሺያ ፌደሬሽን ፓርላማ ሴናተር የተከበሩ ኢጎር መሮዞቭ ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያዩ።

እንደ ዶ/ር በለጠ ሞላ ገለፃ ከአንድ ምዕተ ዓመት ተኩል በላይ የዘለቀውን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚረጋግጥ መልኩ ማስቀጠል ይገባል።

የተከበሩ የራሺያ ፌደሬሽን ሴናተር ኢጎር መሮዞቭ ራሺያ በስፔስ ቴክኖሎጂ፣ በስማርት ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ኒውክለርን ለሰላም በመጠቀም ረገድ፣ በፋርማሲ ቴክኖሎጂ፣ በንግድ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የሁለትዮሽ አገራዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ያላትን አቅም ለማካፈልና ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት መንግስታቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አብራርተዋል። በተለይም የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በራሺያ ከተሞች ሁሉ ለማዳረስ የግሎናስ ዓለምአቀፍ ጂፒኤስ ያስገኘውን ፋይዳ ገልጸዋል።

የተከበሩ ሴናተር ኢጎር ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላና አመራራቸው ሞስኮ በመገኘት የልምድ ልውውጥ ጉብኝት እንዲያደርጉም ጋብዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በመጭው ሰኔ የሚካሄደው አለማቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ክቡር ሚኒስትሩ እንዲገኙ ግብዣ የተላከላቸው መሆኑን ጠቅሰው ሚኒስትሩ እንዲገኙም ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የራሺያ ፌደሬሽን አምባሳደር ኢቭኒ ተርኪያን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ራሺያ በስማርት ሲቲ ፕሮጀክት፣ በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ተግባራትን በአጭር ጊዜ አስቀምጠን ወደ ስራ እናስገባለን ብለዋል፡፡

የኢትዮ ራሺያ የሁለትዮሽ የመንግስታት ፎረምን (Ethio-Russia Intergovernmental Forum) ከኢትዮጵያ በኩል በሊቀመንበርነት እንዲመሩ ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መወከላቸው እንዳስደሰታቸው ክቡር አምባሳደሩ አውስተው በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ይሄው የበይነመንግስታቱ የሁለትዮሽ የጋራ መድረክ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ክቡር ሚኒስትሩም ራሺያን እንዲጎበኙ እንዲሁም የአለማቀፍ የኢኮኖሚ ፎረሙን ለመካፈል የተደረገላቸውን ግብዣ አድንቀዋል።

የራሺያ ፌደሬሽን ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ሁሉ በወሳኝ ግዜያት ከጎኗ መቆሟን ያመሰገኑት ዶ/ር በለጠ፥ የራሺያ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለንዋያቸውን በስፋት እንዲያፈሱና ያልተነካውን የኢትዮጵያ እምቅ አቅም በማውጣት የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በውይይታቸውም ካሁን ቀደም ያሉ ስምምነቶችን በማጠናከር ቀጣይ ግንኙነቶቸን እና የትብብር ማዕቀፍን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን በመለየት ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ለመግባት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook