ወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ራሳቸውንና ሀገራቸውን በሚጠቅም መልኩ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሚዲያ ዘመቻ ለመቀልበስና ተስፋን ለመሰነቅ የሚያስችል “ተስፋ ለኢትዮጵያ” የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ ዘመቻ ተጀምሯል።

ንቅናቄው በአለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ መቀልበስ የሚያስችል እና በሀገራችን በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ጫና ውስጥ የገቡ ዜጎችን ስነ ልቦና ለመገንባት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በንቅናቄው በርካታ ወጣቶች በኢትዮጵያ ላይ ስላላቸው የወደፊት ተስፋ የተመለከተ የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ኢትዮጵያ የዲጂታል አለሙን ጨምሮ በተለያየ መልኩ እየደረሰባት ያለውን አለም አቀፍ ጫና ተቋቁማ እያሸነፈችና ወደ ከፍታዋ እየተጓዘች መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ራሳቸውንና ሀገራቸውን በሚጠቅም መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂውን የገቢ ምንጭ ለማድረግ፣ የሀገራቸውንና የዜጎቻቸውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እና የሀገራቸውን በጎ ገፅታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ሊጠቀሙበት ይገባዋል ብለዋል።

ሳምንቱ የኢትዮጵያን በጎ ነገሮች የሚነገሩበት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት በዜጎች ላይ የደረሰውን የስነ ልቦና ጫና ለማለምለም፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የሀሰት ዘመቻዎችን ለመመከት፣ ሌሎች ሀገራት ስለኢትዮጵያ በጎ መረጃ እንዲይዙና በጎ እንዲያስቡ ለማድረግ ዘመቻ ይደረግበታል ተብሏል።

ሰዎችን የሚያጋጩ፣ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ፣ ተስፋ የሚያስቆርጡና አሉታዊ አሰተሳሰብ ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞችን ማስወገድም የዘመቻው አካል ነው።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook