የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን 46 አገልግሎቶቹን ኦንላይን ለመስጠት የሚያስችለውን ስርዓት አስመርቆ ስራ አስጀመረ፡፡

አገልግሎቶቹ ሙሉ ለሙሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የለሙ ሲሆን የኤሌክትሪክ ስራዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መስጠት፣ እድሳት ማድረግ፣ ምትክ መስጠት፣ አዲስ ጊዜያዊና ቋሚ የኢነርጂ አገልግሎት ኩባንያ ፍቃድ መስጠት፣ ኦን ግሪድ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ፣ ማመንጨትና ማከፋፈያ የስራ ፍቃድ መስጠት፣ ንግድ ፍቃድ ማደስ እና ሌሎችንም የያዘ ነው፡፡

ዛሬ ተመርቀው ወደ ስራ የገቡት አገልግሎቶች አጠቃላይ በኦንላይን የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶችን ብዛት ወደ 331 ከፍ አድርጎታል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ውስጥ ማነቆ የነበረውን የህግ ማዕቀፍ አለመኖር ችግር ለመቅረፍ ፀድቆ ወደ ስራ ከገባው የትራንዛክሽን አዋጅ በተጨማሪ የተለያዩ ህግና መመሪያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውሰጥ የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ባለስልጣኑ የሚጠበቅብተን ሃላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ተወካይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ሞገስ በወረቀት ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች በኦንላይን መሰጠታቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት ለተገልጋዩች ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የለሙት አገልግሎቶች ሳይቆራረጡ ለአገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግና በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook