የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የ17ኛው ዓለምአቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ተሳታፊዎች የበረራ ቲኬት ቅናሽ አደርጋለሁ አለ።

የ17ኛው ዓለምአቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ያሉበትን ደረጃ የተመለከተ ውይይት አድርጓል። የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር በለጠ ሞላ ጌታሁን (ፒኤችዲ) የመሩት የብሔራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ የሶስተኛ መደበኛ ቃለ ጉባኤውን በማጽደቅ በወሳኝ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ መክሯል።

በውይይቱ በዐቢይ ኮሚቴውና ንኡሳን ኮሚቴዎች የተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሪፖርት ቀርቧል። የቪዛ፣ የፕሮቶኮል፣ የጸጥታና ደህንነት የተሳታፊዎች ጥሪ፣ የመረጃ ዝግጅትና ስርጭት፣ የሚዲያ ግንኙነት፣ የጤናና አቅርቦት ዝግጅቶችንና የቅንጅት ስራዎች በቀረቡበት ሪፖርት እስካሁን ከተለያዩ ሀገራት 1300 ያህል ተሳታፊዎች በጉባኤው ለመሳተፍ ማመልከታቸውና መመዝገባቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከልምድ እንደታየው ብዙ ተሳታፊወች ከዚህ በኋላ ባለው ግዜ ጉባኤው ሲቀርብ የሚመዘገቡ እንደሆነ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመላ ዓለም ለሚመጡና በጉባኤው ለሚሳተፉ እንግዶች እስከ 15 በመቶ የአየር ቲኬት ዋጋ ቅናሽ እንደሚያደርግ መግለጹ የቅድመ ዝግጅቱ ስኬታማ ውጤት ተብሏል። አባላቱ ወቅታዊ ዓለማቀፍ የጤና መረጃን በተመለከተ ዓለማቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እንዲዘጋጅ ጠቁመው በባንክና ፋይናንስ፣ በቪዛ በሆቴልና መስተንግዶ በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቁሟል።

አባላቱ በቀረበው ሪፖርት ጥያቄ አቅርበው ተቋማት ከየዘርፎቻቸው የተነሳ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ አራተኛው መደበኛ ስብስባ በዐቢይ ኮሚቴ ሊታዩ የሚገባቸውን ተጨማሪ ተግባራት አቅጣጫ ተቀምጧል። ከአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚክ ኮሚሽንና ከተባበሩት መንግስታት ዓለምአቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ አካላት ጋር ያለው የቅንጅትና የትብብር ስራ የተሻለ መሆኑን ያወሱት የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር በለጠ ሞላ በቀጣይ በበለጠ ጥረትና የተቋማት የጋራ ስራ ለጉባኤው ስኬታማነቱ እንሰራለን ብለዋል።

በመጨረሻው የጉባኤው የቅድመ ዝግጅት ሳምንታት ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ተግባራት አቅጣጫ ያስቀመጡት ክቡር ሰብሳቢው ተቋማት የሚመለከታቸውን ቀሪ ተግባራት በተሻለ ለማጠናቀቅ አልመው እንዲሰሩ መመሪያ ሰጥተዋል። ጉባኤው ኢትዮጵያ ዓለማቀፍ ሁነቶችን የማዘጋጀት ልምዷን ለመላ አገራት የምታሳይበት ነው ያሉት ዶ/ርር በለጠ ተጓዳኝ ሁነቶችን በትኩረት በማዘጋጀት የሚመለከታቸው ዘርፎች አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርጋሉ ብለዋል።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook