የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የባይሎጂካል ጥናት ማዕከል መገንባት የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ በለጠ ሞላ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ኢቪግኒ ተርኪንን በቢሯቸው ተቀብለው አወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ አገራት በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሏቸውን ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

እንደ አምባሳደር ኢቪግኒ ተርኪን ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በቴክኖሎጂው ዘርፍ በርካታ ፕሮጄክቶችን ነድፋ እየሰራች ነው፡፡

ለአብነትም የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ ባይሎጂካል ኤክስፒዲሽንና በምርምር መስክ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።

ክቡር አምባሳደሩ አክለውም በስነ-ህይወት ጥናት፣ በዓሳ እና እንስሳት እርባታ እንዲሁም በአፈር ለምነት ዙሪያም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በሰፔስ ሳይንስ፣ በኒውክሌር ሳይንስ መስኮች እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድም በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለ ጠቁመው የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የባይሎጂካል የጥናት ማዕከል መገንባት የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር አቶ በለጠ ሞላ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሩሲያ ከመቶ (100) ዓመት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያለቸው መሆኑን እንደሚያውቁ አስታውሰው በቀጣይም ካሁን ቀደም በጋራ ስንሰራባቸው ከነበሩት የትብብር ዘርፎች በተጨማሪ ሌሎች የትብብር ዘርፎችንም አካተን እንሰራለን ብለዋል።

ነባር ትብብሮችን በማጠናከር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ሁለቱ ሀገራት ከቆየው ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባሻገር በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመሯቸውን ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም የሩሲያ ፌደሬሽን ሕዝብና መንግስት በአስቸጋሪ ጊዜ ሁሉ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እያደርጉት ለሚገኙት ድጋፍ እና ትብብር አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን የገለጹት ክቡር አቶ በለጠ ሞላ የሩሲያ ሕዝብን መንግስት ድጋፍና ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook