የጀርመን መንግስት ድጋፍ ያደረገለት “የፖስታ አገልግሎት የዲጂታል ፍኖተ ካርታ” ወደ ትግበራ ሊገባ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትና የጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ፖስታ አገልግሎት ለማዘመን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል።

እስከ አሁን የፖስታ አገልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችል ጥናት ሲደርግ ቆይቶ ተጠናቅቋል። በጥናቱ መሰረት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን በዲጂታል መንገድ ለማዘመን የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል ውይይት እየተደረገ ነው።

የትግበራው አካል የሆነውን ስምምነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ)፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ሃና አርያስላሴ እና በጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ቀዳሚ ፀሃፊ ሆልዝፉስ ካሌ ፈርመውታል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) የጀርመን መንግስት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን ለማዘመን እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ በአይ ቲ የሚደገፉ አገልግሎቶችን መስጠት አንዱ ስራ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው የፖስታ አገልግሎት ማዘመን ለኢኮሜርስ አገግልግሎት ጅማሮ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሃና አረያስላሴ የፖስታ ዲጂታል ፍኖተ ካርታው በፍጥነት ወደ ትግበራ እንዲገባ የጀርመን መንግስት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ቀዳሚ ፀሃፊ ሆልዝፉስ ካሌ ከፍኖተ ካርታው ትግበራ በተጨማሪ በቀጣይ በተለያይዩ ጉዳዮች በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የፖስታ አግለግሎት መዘመን የፖስታ እና ጥቅል እቃዎችን ማድረስ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና በማዘመን ወደ ኢኮሜርስ አገልግሎት ለሚደረገው ጉዞ አስተዋፅኦው የጎላ ነው።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook