18ኛው “የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ጉባኤ” በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኤክስቴንሺያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ሞላ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

የቴሌኮም ዘርፍን በከፊል ወደ ግል ማዞር፣ የኤሌክትሮኒክስ መንግስት አገልግሎት መዘርጋት፣ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችንና የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከላትን መደገፍ፣ ኢ-ኮሜርስ፣ የዲጂታል ክፍያ፣ የዲጂታል እውቀት ላይ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል። የፀደቀው የኢ-ትራንዛክሽን አዋጅ፣ በረቂቅ ላይ ያሉት የግል ዴታ ጥበቃ አዋጅ፣ የስታርት አፕ አዋጅ፣ የኢኖቬሽን ፈንድ አዋጅ፣ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ በዘርፉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ ተብሎ እንደታመነባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአይሲቲና ቴሌኮም ዘርፍ ላይ የሚያማክረው ኤክስቴንሽያ ሊሚትድ ዋና ስራ አስኪያጅ ታሪቅ ማሊክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የአፍሪካ ሀገራት የአይሲቲ ዘርፍ ማሻሻያ ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።

በጉባኤው የህግ ማዕቀፎች፣ መሰረተ ልማት፣ ፈጠራ የታከለባቸው የንግድ ስራዎችና አካታችነች ላይ እንደሚመክሩ ተናግረዋል። ጉባኤው አፍሪካን ዲጂታል ለማድረግ፣ በተለያዩ ዘርፎች ተመራጭ እንድትሆን የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የቴክኖሎጂ ተቋማት ኃላፊዎች(ፌስ ቡክ፣ ሊኩይድ፣ …) ፣ የኢምባሲ ተወካዮች እና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ነው።

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Share on twitter
Share on linkedin
Share on facebook